Thursday, February 26, 2015

40ኛ ዓመት የህወሐት የልደት በዓልና ቀውሰኛው የህወሐት አመራር

40 ዓመት ወደ ውሃላ በዓይነ ህሊና ተመልሰን ስንመለከት ብዙ ነገር በአእምሮአችን ይደቀናል፡፡ በዚያን ጊዜ ወጣቱ የደርግን ፋሽስታዊ ተግባራት ለመመከት፤ተማሪው ከትምህርት ገበታው፣አስተማሪው፣መንግሥት ሠራተኛው ከቢሮው፣ ገበሬው ሞፈሩን ጥሎ ወታደራዊውን ደርግ ለመፋለም በረሃ ገባ፡፡ ይህ ወጣት በተሰማራበት መስክ ደርግን በመመከት በ17 ዓመታት መራራና በተራዘመ የትጥቅ ትግል ለመገርሰስ በቃ፡፡ያለ መስዋእትነት ድል አይታሰብምና ብዙ ወጣቶች ለህዝብ ብለዉ በየሸንተረሩና ታራራው ተቀብሩ፡ብዙ ወጣቶች አካለ ጉዳተኛ ሆነዋል፡፡በዚያ ብዙ ውጣ ውረድ በተሞላበት መራራና የተራዘመ የትጥቅ ትግል ትግሉ አንቱ የተባሉ ብዙ ወታደራዊና ፖለቲካዊ መሪዎችን ለማፍራት ችለዋል፡፡
አሁን ይህንን ታሪካዊ ጉዞ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ቆይቶ በዓሉ ተጠናቅቀዋል፡፡ ህዝቡና ቅን ልቦና ያለዉ ሁሉ በዓሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለበት ብሎ የሚለው ኖሯል፡፡
ይህ በዓል አዲስ መንፈስ በሚፈጥር ሁኔታ መከበር ነበረበት፡፡ ይህንን የ17 ዓመት የትጥቅ ትግል አሁን በህይወት የሌሉና በህይወት እያሉም በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የራሳቸው መንገድ የያዙ ነገር ግን በትጥቅ ትግሉ ትልቅ ሚናና የመሪነት ቦታ የነበራቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ የትጥቅ ጉዞው የነዚህ ሰዎች ድርሻ ነበረው፣ለድል እንዲበቃ የራሳቸው ድርሻ ተጫውተዋል፡፡ ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ነበረበት፡፡ ይህንን የ40 ዓመቱ የህዝቡ በዓል የህዝቡን ተሳትፎ ማዕከል አድርጎ፣ትግሉን የማደስ ግብ ይዞ መነሳት አለበት፡፡ ይህንን ዕድል ተጠቅሞ የድሮውን የቅንነት ወኔና ለህዝብ ብሎ መታገል እሴት ማሳደስ ይቻል ነበር ፡፡ወጣቱ ሙስናን መዋጋት ይችል ዘንድ ማነቃነቅ ይቻል ነበር፡፡ ለህዝብ ብለዉ የተሰዉ ታጋዮችን ታሪክ በባለ ታሪኮች በማቅረብ የቆሰለውን አእምሮ ማሳደስ ይቻል ነበር፡፡ ደርግን የደመሰሰ ሃይል አሁን በአንድ መስመር እየተጓዘ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ከትጥቅ ትግሉ ድል በውሃላ የፖለቲካ ልዩነቶች ተፈጥረው በአንድ ሃዲድ መራመድ ቆመ፡፡ ይህ ለጥላቻና እኔን የረገጥኩትን መሬት መርገጥ የለብህም እስከ ማለት የሚያደርስ አይደለም፡፡ አባቶቻችን በመሬት የይገባኛል ጥያቄ ተካስሰው ውሳኔው የዳኞች ነው ብለው ከችሎት ወጥተው አብረው በአንድ ሲበሉና ሲጠጡ፣ አዲስ አበባ ለይግባኝ ሲሄዱ አብረው ፣በሄዱበት ቦታ ሲያድሩ አብረውና ለድህንነታቸው እርስ በራሳቸው እየጠበቁ ያድሩ ነበር፡፡ ከዚህ ጥልቅና በሳል እሴት መማር ይቻላል፡፡ የካቲት 11 40ኛ ዓመት ጊዜ ስናከብር እነዚህን እሴቶች የሚያዱስበት አጋጣሚ መጠቀም ይቻላል ፡፡ ለህዝቡና ለትግሉ ጠቀሜታ ተብሎ፡፡
ታሪኩ የነዚህ በህይወት የሌሉና በህይወት ኖረውም የራሳቸው የፖለቲካ መንገድ የያዙም ጭምር ነው፡፡የነዚህ ሁሉ ታጋዮች ድምር ውጤት ነውና በሬድዮ ይሁን በቴሌቭዥን የሚቀርበው ገለጻ ይህንን ግምት ውስጥ ማስገባት ነበረበት እላሎህ፡፡ የሽልማቱ ስነሥርዓቱም እንዲሁ፡፡
ለምን ?
1) አንደኛ እውነቱና ሀቁ እሱ ስለሆነ፣
2_) ይህንን ማድረግ ካለፉ ሥርዓቶች የታሪክ አጻጻፍ የተለየና ሀቀኛ ታሪክ ያደርገዋል፡
3) ይህ ማድረግ የድሮ የጓደኝነት መንፈስ እንዲፈጠር ያደርጋል፡የተረሳውን የመፈቃቀርና የመተባበር መንፈስ ጭሮ የሰማእታትን አደራ የካደ ለሆዱ ያደረ ሁላ በሚፈጠረው የቀድሞ የታጋዮች መንፈስ እንዲለበለብና አዲሱን የመተጋገዝና ለህዝብ ብሎ አሁንም የመሥራት ህሊና ጎልብቶ እንዲወጣ ዕድል ይሰጣል፡፡
ነገር ግን ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ ካለፉት ስርዓቶች የታሪክ አገላለጽ የተለየ እየሆነ አይደለም፡፡የግለሰቦች ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአንድ አከባቢ ታሪክ ሆኖ እንዲቀርብ እየተደረገ ነው፡፡ የትግሉ ፈጣሪና የድሉ መሃንዲስ መለስና መለስ
ሆኖ ሲቀርብ እያየን ነው፡፡ ነገር ግን ከመለስ በላይ ብቃትና የአመራር ችሎታ የነበራቸው ታጋዮች መርተውት ነው የትጥቅ ትግሉ ለድል የበቃው፡፡አቶ ግደይ ዘርዓፅዮን በ1977 ዓ፡ም ያነሱት ሐሳብ ድርጅቱ ሲቃወመው፤አሁን የሳቸውን ሐሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ሲያደርግ ያለ ምስጋና ነው፡፡ የሰዎችን ሐሳብ በመቅዳት የራስን አስመስሎ ማቅረብ በህወሐት ታሪክ የተለመደ ቅጥፈት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የታሪኩ አቀራረብ ካለፉት ሥርዓቶች የተለየ መሆን ነበረበት፡፡ታሪኩ የጋራ ስለሆነ ነው፡፡ ያንን መድገም አልነበረበትም፡፡በዚህ የትጥቅ ትግል ቢያንስ እነ ግደይ ዘርዓጽዮን፣አረጋዊ በርሀ፣አረጋሽ አዳነ፣ አውዓሎም ወልዱ፣እነ ተወልደ ወልደማርያም፣እነ አለምሰገድ ገብረአምላክ፣ እነ ገብሩ አስራት፣እነ ስዬ አብርሃ፣እነ ኢታማጆር ሹም ጻድቃን ገ\ተንሳኤ፣አስገደ ገ\ሥላሴ ስለበዓሉ ተጠርተው መግለጫ እንዲሰጡ መደረግ ነበረበት፡፡ አስገደ ገብረ ሥላሴ ከመሥራች ታጋዮች አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ አሁን በስልጣን ያሉ ሰዎች አስገደ መሥራች እንዳልሆነ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ አስገደ መሥራች ብቻ ሳይሆን ለመሥራቾች ወታደራዊ ስልጣና የሰጣቸውም እሱ ነው፡፡ለትጥቅ ትግል አመች ቦታ በመምረጥም ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ አስገደ የወላጆቹ ስም ወላይ ነው፡፡ አስገደ የትግል ስሙ ነው፡፡ አስገደ ማለት በትግርኛ ቋንቋ በቁጥጥሩ ሥር አዋለ፣አምበረከከ ማለት ነው፡፡ ይህንን ስም የተሰጠው ባደረገው የጀግንነት ተግባር ነው፡፡ እንደዛሬ አያደርገውና ፤አቶ መለስ አንድ ጊዜ በሃገረሰላም የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ታጋዮች በተሰበሰበቡት ወቅት በድርጅታችን ውስጥ አስገደን የሚያክል ጀግና የለም ብለው ነበር፡፡ አቶ ስብሐትም መነሻው ለክፋት ብለው ቢሆንም እኔ የሚወስነው ሁላ አስገደን ሳላማክር ወስኜ አላቅም ብለዉ ነበር፡፡ እንደነዚ ዓይነት ሰዎች ናቸው እንግዲህ ከታሪኩ እንዲፋቁ እየተደረገ ያለው፡፡ የዚህ መነሻ ደግሞ የሌሎችን ጎሳዎች ተራ በማንቋሸሽ የነሱን ጎሳ የታሪኩን ባለቤት አድርጎ ለመሰነድ ነው፡፡ ይህንን ባለፉት ሥርዓቶች እየተሰራበት የመጣ ነው እነዚህም ይህንን እየደገሙ ይገኛሉ፡፡
የካቲት 11ና ሐየሎም አርአያ አይለያዩም፣ሐየሎም አርአያና ድል ተለያይተው አያውቁም ፡፡በዚሁ ታሪካዊ በዓል ታደያ የሐየሎም አርአያ ሚና ጎልቶ እየተዘከረ አይደለም ፡፡ ለምን እንደሱ እየተደረገ እንዳለ ምስጢሩ መረዳት አስቸግሮ ነበር፡፡ የአሁን አሁን ግን በሚናፈስ ወሬ ምክንያቱ መረዳት ትችለዋል፡፡ ሆን ተብሎ በወሬ እንዲናፈስ እየተደረገ ያለው በጣም የሚገርም ነገር ነው፡፡ ሐየሎም አርአያ ህዝብና አገር ከድቶ በየመጠጥ ቤቶችና ሴቶችን እያደና የተገደለ ሰው ስለሆነ በዚሁ የ40ኛው ዓመት የየካቲት 11 በዓል ማንሳት አስፈላጊነት የለውም ተብሎ ለሚድያ ሰዎች ተነግሮ በዚህ ምክንያት በቴሌቭዥንና በሬድዮ ስሙ እንዳይነሳ መደረጉ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ይህ አካሄድ ታሪክን የአንድ አካባቢ ታረክ ሆኖ እንዲወጣ የማድረግ ስልት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሐየሎም እንዴት እንደተገደለና ማን እንደገለው ግልጽ ነው፡፡ ያኔ የተገደለበት ምሽት ከቤቱ በፕሮፌሰር እንድርያስ ተጠርቶ ደክሞኛ ዛሬ መውጣት አልፈልግም እያለ ለኔ ብለህ መድከም አለብህ ተብሎ ለሰው ክብር ብሎ ወጥቶ እንዲገደል መደረጉ ሐየሎም ማን ገደለዉ በሚል ርእስ የተጻፈው ምስጢራዊ ጽሑፍ ሳናነብ አንቀርም፡፡ ሁኔታው እንዲህ እያለ ሐየሎም አገርና ህዝብ ከድቶ በማይረባ ነገር የሞተ ነው ተብሎ በህዝቡ ዘንድ እንዲወራ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የአካል ጉዳተኞችም እንዲሁ፡፡
የትጥቅ ትግሉ ታሪክ ብዙ ቦታ ሳንጓዝ በአንድ ቦታ ላይ እናገኘዋለን፡፡ ይህም በትጥቅ ትግሉ ትልቅ ሚና የነበራቸውና በዚህ ወላፈን ተጠብሰው አካለጉዳተኛ ሆነው ያሉ አርበኞች በመቀለ ቀበሌ 1803 ይገኛሉ፡፡ከነዚህ ብርቅዬ ጓዶች ሁሉም ነገር አንድ ሳይቀር ታሪኩን ማቅረብ ይቻላል፡፡ እነዚህም ግምት ማስገባት በተቻለ ነበር፡፡
የሽልማቱ ቁምነገር ስንመለከት ደግሞ፡
ሽልማቱ ለተራ ታገዮች በጀግንነታቸው የሚታወቁ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ መሪዎችን ያማከለ ሽልማት ነው፡፡ ይህንን አካሄድ በቀድሞ ገዥዎቻችን የነበረና የተለመደ ነው፡፡ ህወሐት ይህንን እየደገመ ነው፡፡ በኢድዩ፣በኢህአፓና በደርግ በተደረጉ ውግያዎች አንድ እግራቸው በብሬን ተቆርጦ የተቆረጠውን እግራቸው አንስተው በርቱ ጓዶች፣ ብለው የዓላማ ፅናት ለሌላው ታጋይ ትምህርት ሰጥተው የተሰዉ፣ፈንጂ ረግጠው ለመሰዋት ራሳቸውን አስቀድመዉ የተሰዉ ታጋዮች ተረስተው መሪዎችን መሸለም የድሮ ገዥዎችን ታሪክ መድገም ነው፡፡
ይህንን ሁኔታ አቶ ዓባይ ወልዱ በትግርኛ ባቀረቡት በዓሉን አስመልክተው ባቀረቡት መግለጫ በትክክል ገልጸውታል፡፡ ይኸውም፡ ትግላችን ድሀው አንደቱን ቀና ብሎ እንዲናገር ሃብታሙ ደግሞ ሃብቱን አሰማርቶ እንዲበለጽግ አስችለዋል ብለዋል፡፡ አቶ ዓባይ ይህንን ሀቅ ሳይደብቁ መናገራቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ይህንን አገላለጽ ግልጽ ነው ፡፡ ድሀው

የመናገር መብት አግኝተዋል፡፡ እሱም ገዥው ፓርቲውን ለማሞጎስ፣ሃብታሙ ደግሞ ከመንግሥት በላሥልጣኖች በመጠጋት የአገሪቱን ሀብት በቁጥጥሩ ሥር በማስገባት በድሀው ተጠቃሚነቱን በላቀ ማረጋገጥ ችለዋል ማለታቸው ነው፡፡ በኢህአዴግ|ህወሐት ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ማለት ይህ ማለት መሆኑ አቶ ዓባይ በግልጽ ነግረውናል፡፡
በጣም ከሚያስገርመው ነገር አንዱ ደግሞ፡ ህወሐት ለትግራይ ህዝብ መሸለሙ ነው፡፡ የዚህ መነሻ ሐሳብና ተግባር ህወሐት በህዝብ ላይ ያለውን ንቀት በግልጽ ያመለክታል፡፡ ሸላሚ ህወሐት የሽልማቱ ተቀባይ ህወሐት አስገራሚ ነገር ፡፡ ህወሐት እያበደ መሆን አለበት፡፡ የሆነ ቀውስ ውስጥ እንደገባ ያመለክታል፡፡
ስለ የመንግሥት ሀብት መባከኑ የተለመደ ስለሆነ ነው እንጂ በመንግሥት ገንዘብና ንብረት ነው በዓሉ የተከበረው፡፡ በትግራይ ውስጥ ከ800 በላይ ቀበሌዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ቀበሌዎች 65 ሰዎች ከአንድ ቀበሌ በበዓሉ እንደገኙ ተደርገዋል፡፡ የነዚህ ውል አበልና ትራንስፖርት የየወረዳው በመንግሥት በጀት የተሸፈነው፡፡ ከዚህ ተጨማሪ ከህዝቡ ገንዘብ እንዲዋጣ ተደርጎ ነው የተፈጸመው፡፡ የመንግሥት መኪናዎች በሙሉ ለሁለት ወር ያህል በዓሉን ለማድመቅ ተብሎ በድርጅቱ ሥራ ነው ተሰማርተው የከረሙ፡፡ ይህንን በጀትም የመንግሥት ነው፡፡ በበዓሉ ቀን ተሰልፈው የነበሩ በጣም ብዙ መኪኖችና በዓሉን ለማድመቅ ተብሎ የተዘጋጁ የተለያዩ ምስሎች በጣም ብዙ ገንዘብ ወጭ ተደርጎባቸው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ይህም የመንግሥት በጀት ነው፡፡ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሰዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ጸጥታ ከማክበር በዘለለ ልክ የመንግሥት በዓል በሚመስል ሁኔታ የፖሊስ ማርሽ ባንድ ተሰልፈው እንዲያከብሩ ተደርገዋል፡፡ ይህንን ወጭም ከመንግሥት ነው፡፡ ህወሐት በዚህ በዓል ያላሳተፈው መከላክያ ብቻ ነው፡፡ ስቪል ለብሰው የገቡ ነበሩ፡፡ ተዋጊ አውሮፕላን በበዓሉ ዋዜማ በመቀሌ የሰማይ ክልል ዋኝተዋል፡፡ ይህንን አካሄድ አስነዋሪ ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ ይህንን እያየ ዝብሎ ማየት የለበትም፡፡ ታሪኩ የግለሰዎች ታሪክ እየተደረገ ነው፡፡ የአንድ አከባቢ ታሪክ ብቻ ተደርጎ እየተጻፈና እየተነገረ ይገኛል፡፡ ይህንን እኩይ ተግባር ህዝቡ፣ ወጣቱና ምሁራኑ ሊዋጉት ይገባል፡፡
ለዚህ ሁሉ ጠንቅ እሆነ ያለዉ የፖለቲካ ልዩነት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካና የሐሳብ ልዩነት እንዳላቸው ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በሬድዮ ይሁን በቴሌቪዥን ጠርቶ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እየሰጡት ያሉ መግለጫ እነሱም እንዲሰጡ ማድረግ ሐጢአቱ የቱ ላይ ነው ? ይህ ማድረግ እንደኔ እንደኔ በሳልነትና አስተዋይነት ነው ፡፡ የፖለቲካና የሐሳብ ልዩነት ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚያገናኝ ነገር የለውም፡፡ በዚህ በሰለጠነ ዓለም በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት በአንድ መአድ መብላትና ስለልዩነቱ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መጫወት ይቻል ነበር እንኳንና በዚሁ በዓል ፡፡

ከአማን ነጋሲ ከመቀሌ ትግራይ
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com February 24, 2015 

No comments:

Post a Comment